undefined undefined undefined undefined

    Get Appointment

    CircleCircle
    BlogMarch 7
    የኢፊዲሪ ትምህርት ሚኒስቴር ከደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ጋር ተወያየ።
    (የካቲት 27/2017 ዓ.ም ) የኢ.ፌዴሪ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋና የምንስትሩ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ከደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ጋር ውይይት አደረጉ፡፡
    የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተ/ፕሬዚዳንት ታደሰ ረጋሳ(ፒኤች.ዲ) እንኳን ወደ ደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ በሠላም መጣችሁ በማለት የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮችን በዩኒቨርሲቲው በአካል በመገኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸው የዩኒቨርሲቲው ወቅታዊ ሁነታ፣ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት እና የወደፊት አቅጣጫዎች ላይ ለመወያየት እንዲሁም አስፈላጊ ድጋፍና ክትትል መስጠት ለዩኒቨርሲቲዉ አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
     
    በዩኒቨርሲቲው የአካ/ም/ቴ/ሽ/ና ማ/አ/ም/ፕሬዝዳንት ተወካይ ረዳ ነሞ(ፒኤች.ዲ) ደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ የተጣለበትን አገራዊ ተልዕኮ ለመወጣት እየተሠሩ ያሉ ሥዎችንና ያጋጠሙትን መሰናክሎች አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል። በገለፃቸውም ዩኒቨርሲቲው በማስተማር፣ በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት እያደረገ ያለውን ጥረት፣ እንዲሁም የመሰረተ ልማት ግንባታውንና ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች ጠቁመዋል። የክትትልና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ አስፈላጊ ከመሆኑ ጋር በቂና ውጤታማ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
     
    በውይይቱም የኢፊዲሪ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስቴር ፒሮፌሴር ብርሃኑ ነጋ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲዎች ለመማር፣ ለማስተማር እና ለምርምር የተሰጡ ተቋማት ሆነው በመንቀሳቀስ እውነተኛ የእውቀት ማዕከል ሆነው ማገልገል እንዳለባቸው አሳስበዋል። በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የአመራር፣ የአስተሳሰብና አጠቃላይ የባህል ለውጥ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፣ የአመራር መዋቅርን ለመቀየር ከወዲሁ ጥረት መደረጉን ጠቁመዋል። ዩኒቨርሲቲዎች የህብረተሰቡን ህይወት ለመለወጥ እና አገራዊ ችግሮችን ለመፍታት የአካባቢያቸውን ጠንካራ ጎን በመገንዘብ አግባብነት ባለው ጥናትና ምርምር ላይ በመሳተፍ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው አስረድተዋል። በዚህ ጠቃሚ ተግባር የአካዳሚክ ምሁራን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
     
    በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ የአስተዳደራዊ ጉዳዮች መሪ ሥራ አስፈፃሚ ሰለሞን አብርሃ (ዶ/ር) በዩኒቨርሲቲው ክትትል ወቅት የተለዩትን ጥንካሬዎችና ማሻሻያ የሚሹ ጉዳዮችን ለውይይት መነሻ አቅርበዋል። አዲስ የተወከሉ አመራሮች የተጀመሩት ሥራዎችን በጥንቃቄ በመገምገም የትምህርት ጥራትን የሚያጎለብቱ ጉዳዮችን በማስቀደም ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለባቸዉ አሳስበዋል።
     
    የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኮራ ቱሹኔ ዩኒቨርሲቲዎች ሀብታቸውን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመጠቀም ቁልፍ ጉዳዮችን በመለየት በተደራጀ መንገድ መፍታት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። አዲሱ አመራር ለትምህርት ጥራት ማሳደግ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባም አሳስበዋል። በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው የሚያደርጋቸውን የሚደነቁ ተግባራት አምነው ተቋሙ የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች ለመፍታት በትምህርት ሚኒስቴርና በዩኒቨርሲቲው ቦርድ መካከል ያለው የተሻሻለ ቅንጅት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
     
    የዉይይቱ ተሳታፊዎች ባነሱት ሃሳብ የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ 4ኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲ መሆኑን ጠቅሰዉ በተለያዩ ተግዳሮቶችን ተቋቁሞ የመማር ማስተማር፣የማህበረሰብ አገልግሎትና ጥናትና ምርምሮችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል። በመሆኑም ከነባር ዩኒቨርሲቲዎች ደረጃ መታየት እንደለለበት እና የትምህርት ሚኒስቴር ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።
    በመጨረሻም የዩኒቨርሲቲው ተ/ፕሬዝዳንት ታደሰ ረጋሳ(ፒኤች.ዲ) በትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተሳትፎ ወሳኝ የሆኑ ድጋፎችን ለማድረግና ተጠያቂነትን ለማስፈን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው በመግለጽ የአመራር ሽግግሩን ተከትሎ ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ጥራት ፕሮግራሞችን በማሳደግ ላይ በትኩረት እየሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል። 
     
    በተጨማሪም የዩኒቨርሲቲውን ተልእኮ ወደሚፈልገው የላቀ ደረጃ ለማድረስ አካሄዳችንንና አሰራሮቻችንን በማሻሻል አቅማችንን በተሟላ ሁኔታ መጠቀም ይጠበቃል ብለዋል።
     
    Facebook:https://web.facebook.com/daduempower